Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎች ዋነኛ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየሠራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጎነት ቁጥር 3 ተብሎ በተሰየመው የመኖሪያ መንደር የተገነባውን ባለ አምስት ወለል ዘመናዊ የመኖሪያ ሕንጻ መርቀው ለአቅመ ደካሞች አስተላልፈዋል።

ቤቶቹ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ገብስ ሰፈር በሚባለው የመኖሪያ መንደር ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞችና ለተለያየ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች ተላልፈዋል።

ለነዋሪዎቹ 54 የመኖሪያ ቤቶች የተላለፉ ሲሆን÷ ሳሎን፣ መኝታ፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት÷ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎች ዋነኛ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን 270 ሺህ ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ማስተላለፉን አስታውሰው÷ ከዚህ ውስጥ 39 ሺህ ቤቶች የተገነቡት በበጎ አድራጊ ባለሃብቶች መሆኑን ተናግረዋል።

የዜጎችን ህይወት የመቀየር ሥራ በመንግስት በጀት ብቻ ስለማይሳካ በርካታ ልበ ቀና ባለሃብቶችና አቅም ያላቸው ዜጎች ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ለመሥራት ውጥን መያዙን አረጋግጠዋል።

ከንቲባዋ በዛሬው ዕለትም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በአንዱዓለም ተስፋዬ

Exit mobile version