Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በውሃ ሃብት አጠቃቀም ተጽዕኖ በሚያደርሱ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ በመሆን ለብክለት እና ብክነት መንስዔ የሚሆኑ አካላት ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የከርሰ ምድር ውሃ በሂደት እያለቀ የሚሄድ እንደሆነ ተናግረው፤ በትላልቅ ኩባንያዎች ጭምር የከርሰ ምድር ውሃ የሚያልቅ ግብዓት ተደርጎ አይወሰድም ብለዋል።

የከርሰ ምድር ውሃ ጉዳይን በተመለከተ ግንዛቤ እና አቅም የመፍጠር ስራ መሰራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሃብት ከብክለት እና ብክነት ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ወደ ተግባር መገባቱን እና ተጠቃሚ አካላት በተጠያቂነት እንዲጠቀሙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ በመሆን ለብክለት እና ብክነት መንስዔ የሚሆኑ አካላት ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱ ኢንዱስትሪዎች ሕግ ወጥቶ በጥብቅ ደንብ እና መመሪያ መተዳደር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎች ለሀገር እድገት ጠቃሚ እንደሆኑና አካባቢውን በማይጎዳ መልኩ መስራት እንዳለባቸው በዓለም አቀፉ የአካባቢ ህግ መደንገጉን ችሮታው (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ ተፈጥሯዊ አማራጮችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል እና ዘላቂነት ያለውን አስተዳደር መከተል እንደሚያስፈልግ አንስተው÷ መንግስትም ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የሕግ ተጠያቂነት እና በሕግ የመገዛት ስርዓቱ ሊጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ውሃ ከከርሰ ምድር እየተጠቀሙ ቢሆንም በወሰዱት ልክ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲያገግም ለማድረግ ደግሞ የቴክኖሎጂና የባለሙያው ድጋፍ አናሳ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ሙሉጌታ ዳዲ (ዶ/ር) ናቸው።

የከርሰ ምድር ውሃ እንዲያገግም ለማድረግ ሁለት መንገዶች መኖራቸውን አንስተው÷ ውሃን ማሳለፍ በሚችሉ የምድር ገጾች በኩል ውሃ እንዲገባ ማድረግ አንደኛው አማራጭ እንደሆነ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ አይነት ልማቶችን በማከናወን በተፈጥሯዊ ሂደት የከርሰ ምድር ውሃ እንዲያገግም ማድረግ ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version