አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ድግግሞሽን ለመቀነስና ወደ ዜሮ ለማውረድ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ የሚዲያ ማኔጅመነት ሃላፊ አቶ አብርሃም ደግፍ እንዳሉት ÷በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የሚያጋጥሙ የኃይል መቆራረጥ ችግሮችን ወደ ዜሮ ለማውረድ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ፡፡
በእቅዱ መሰረት አዲስ አበባ ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው÷ይህንን ተሞክሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በማውረድ የኃይል መቆራረጥ መንስኤዎችን የመለየትና የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ 152 መካከለኛ መሥመሮች ላይ ምርመራ መካሄዱን ሃላፊው ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም መካከለኛ መሥመሮቹን የሚሸከሙ 49 ሺህ 581 ምሰሶዎች ላይ ቅድመ ምርመራ መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡
በዚህም ከ26 ሺህ 559 በላይ ከባድና ቀላል ችግሮች የተገኙ ሲሆን ÷ ተጨማሪ የሃይል መቆራረጥ መንስዔዎችን የመለየቱና መፍትሔ የመስጠቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በመዲናዋ 7 ሺህ 521 ቦታዎች ላይ የዛፎች ንክኪ፣ 6 ሺህ 399 መቀየር የሚያስፈልጋቸው ምሰሶዎች፣ 6 ሺህ 338 የረገቡ እንዲሁም 2 ሺህ 427 መሥመሮች ከግንባታዎችና እርስ በርስ የተቀራረቡ ሆነው መገኘታቸውን ተጠቅሷል፡፡
ይህም ለተደጋጋሚ የሃይል መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑ ዋነኞቹ የግኝት ነጥቦች መካል ተጠቃሽ ነው ያሉት አቶ አብርሃም ÷እስካሁን ለ7 ሺህ 663 ያህሉ አስፈላጊው ማስተካከያ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ የሃይል መቆራረጥ ድግግሞሽን ለመቀነስና ወደ ዜሮ ለማድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በመዲናዋ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስና በሚከናወነው የሥራ ሒደት ላይ ማሕበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

