Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ማንቼስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐር …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐርን ያገናኘው ተጠባቂው የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4 ሠዓት ላይ በቢልባኦ ከተማ በሚገኘው ሳን ማሜስ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

በዚህ የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው ማንቼስተር ዩናይትድ፤ በዩሮፓ ሊግ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ለፍፃሜው በቅቷል።

በሩብ ፍፃሜው ከሊዮን ጋር በተደረገው ጨዋታ ባለፉት ዓመታት በክለቡ ደጋፊዎች ሲተች የነበረው ሀሪ ማጓየር ያስቆጠራት ጎል ዩናይትድን ወደ ግማሽ ፍፃሜው አሻግራለች፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በዩሮፓ ሊግ በግማሽ ፍፃሜው ይፈተናል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ተጋጣሚውን የስፔኑን ክለብ አትሌቲክ ቢልባኦን በድምር ውጤት 7 ለ 1 መርታት ችሏል፡፡

18 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን የተሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም፤ “የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ብናነሳ እንኳን መጥፎውን የውድድር ዓመት አይቀይረውም፤ እጅግ በጣም መጥፎ ጊዜ እያሳለፍን ነው” ብለዋል፡፡

ቀያይ ሰይጣኖቹ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፋቸውን ቦታ ለማግኘት ቶተንሃም ሆትስፐርን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአሰልጣኝ አንጂ ፖስቴኮግሉ የሚመራው ቶተንሃም ሆትስፐር በበኩሉ፤ ይህን ዋንጫ አሳክቶ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ለማረጋገጥ ዩናይትድን ለመርታት ይፋለማል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐር፤ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 21 ጨዋታዎችን ተሸንፏል።

በሌላ በኩል በዩሮፓ ሊግ በሩብ ፍፃሜው አይንትራክት ፍራንክፈርትን፤ በግማሽ ፍፃሜው ደግሞ ቦዶ ግሊምትን በመርታት ለፍፃሜ መድረስ ችሏል።

ይህ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ አሰልጣኝ ፖስቴኮግሉ በየትኛውም ክለብ በሁለተኛ የውድድር ዘመናቸው ዋንጫ የማሳካት ልምድ እንዳላቸው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ወጥ ብቃት ባለማሳየታቸው በብርቱ እየተተቹ ያሉት ሁለቱም ቡድኖች፤ በዩሮፓ ሊግ ስኬታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ለፍፃሜ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡

የማንቼስተር ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች አማድ ዲያሎ፤ ቡድናቸው የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ለማሸነፍ ሁሉንም እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡

እንዲሁም የቶተንሃም ሆትስፐር ተጫዋቾች፤ ለዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ መድረሳቸው በሕይወታቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፤ ዋንጫውን ከፍ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ እንደሚደርጉ ተናግረዋል፡፡

የሪያል ማድሪድ እና ቶተንሃም ሆትስፐር የቀድሞ ተጫዋች ዌልሳዊው ጋሬዝ ቤል በዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ በተጋባዥ ተንታኝነት ይገኛል፡፡

ጉዳት ላይ የነበሩት የቀያይ ሰይጣኖቹ ተጫዋቾች፤ ጆሽዋ ዝርኬዚ፣ ሌኒ ዮሮ እና ዲያጎ ዳሎት ትናንት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሠርተዋል፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በፈረንጆቹ 2017 የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ እየተመራ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሳካቱ ይታወሳል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version