Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሃሪ ኬን እና ዋንጫ የታረቁበት የውድድር ዓመት…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአርሰናል አካዳሚ ተጫዋች በነበረበት ወቅት የስፖርት አቋም የለህም ተብሎ ተባርሯል፡፡

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ከአለን ሺረር በመቀጠል ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ቢሆንም በሊጉ በቆየባቸው ዓመታት ግን ከዋንጫ ጋር መገናኘት አልቻለም።

በቶተንሃም ሆትስፐር ባደረጋቸው 438 ጨዋታዎች 270 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፥ በሀገረ እንግሊዝ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎችና ጎል አስቆጣሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ለበርካታ ጊዜያት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአመቱ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ሀሪ ኬን በቶተንሃም ሆትስፐርስ ቤት ከ11 ዓመታት በላይ ክለቡን አገልግሏል።

ተጫዋቹ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ዝናን ካተረፉ እንደ ዋይን ሩኒ፣ ሰርጂዮ አጉዬሮ፣ ቲየሪ ኦነሪ የመሳሰሉ አጥቂዎች ከፍ ያለ ጎል የማስቆጠር ሪከርድ ቢኖረውም በሊጉ በቆየባቸው ዓመታት አንድም ዋንጫ አለማሸነፉ የብዙዎች ጥያቄና አሳዛኝ ታሪኩ ነው፡፡

ሀሪ ኬን የዋንጫ ጥሙን ለመቁረጥ ሌሎች ክለቦችን መመልከት ጀመረ፡፡ ማንቼስተር ሲቲዎች ኧርሊንግ ሀላንድን ወደ ክለቡ ከማምጣታቸው በፊት ኩን አጉዬሮን የሚተካላቸውን አጥቂ ፍለጋ ወደ ገበያ ሲወጡ ሀሪ ኬን የአይናቸው ማረፊያ ነበር፡፡

ውሃ ሰማያዊዎቹ አንጋፋውን አጥቂ ሀሪ ኬንን ለማስፈረም ጥረት ሲያደርግ፥ ተጨዋቹም የዋንጫ ጥማቱን ለማስታገስ ወደ ኢትሃድ ለመኮብለል ፍቃደኛ ነበር፡፡

ሆኖም ስፐርሶች ኬንን ለመልቀቅ ከሲቲ ጋር ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ተጫዋቹ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ከቶተንሃም የልምምድ ሜዳዎች መቅረት ጀምሮ ነበር።

ቶተንሃሞች እንደማይለቁት አበክረው ከነገሩት በኋላ በሰሜን ለንደኑ ክለብ ለመቆየት የተገደደው እንግሊዛዊው አጥቂ፥ በመጨረሻም ወደ ቡንደስሊጋው በማቅናት የጀርመኑን ሃያል ክለብ ባየርን ሙኒክን ተቀላቅሏል፡፡

በባቫሪያኑ ቤት የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው ለበርካታ ዓመታት በቡንደስሊጋው የበላይ ከሆነው ባየርን ሙኒክ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ እንደሚያሳካ በበርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ቢጠበቅም የታሰበው ሳይሆነ ቀረ፡፡

ባየርን ሙኒክ ለተከታታይ 11 አመታት የሊጉን ዋንጫ ያለ ማንም ተቀናቃኝ ማሳካት ቢችልም ሀሪ ኬንን ባስፈረመበት የውድድር ዘመን ግን የቡንደስሊጋውን ዋንጫ በባየር ሊቨርኩሰን ተነጠቀ።

የጀርመኑ ሀያል ክለብ ከረጅም ዓመታት በኋላ በ2023/24 የውድድር አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ዋንጫ ለማጠናቀቅ ተገደደ።

በርካታ የስፖርት ቤተሰብም የኬን የዋንጫ እርግማን ጀርመን ድረስ ተከትሎት እንደሄደና ሙኒክን ዋንጫ እንዳሳጣው መናገር ጀመረ።

በዚያ የውድድር አመት ምንም እንኳን ባቫርያኑ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያለ ዋንጫ አመቱን ቢቋጩም ኬን በቶተንሃም ሆትስፐር ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ ጎሎችን ማስቆጠሩን አላቆመም ነበር፡፡

በቡንደስሊጋው 36 ጎሎችን ሲያስቆጥር በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ 8 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው እንግሊዛዊ አጥቂ በአጠቃላይ በሁሉም ውድድሮች ለባየርን ሙኒክ በ45 ጨዋታዎች 44 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በሬንጅ ሮቨርስ አካዳሚ መጫወት የጀመረው ሀሪ ኬን በመቀጠልም የቶተንሃም ባላንጣ ጎረቤት የሆኑትን የአርሰናል የወጣቶች አካዳሚን መቀላቀል ችሎ ነበር፡፡

በወቅቱ የአርሰናል አካዳሚ ሃላፊ የነበሩት ሊያም ብራንዲ ኬን አርሰናልን እንዴት እንደለቀቀ ሲናገሩ፥ የስፖርት አቋም የለውም ተብሎ የወቅቱ የመድፈኞቹ አለቃ በነበሩት አርሰን ቬንገር መሰናበቱን አስታውሰዋል፡፡

ቶተንሃም ሆትስፐርን ከመቀላቀሉ በፊትም በሌስተር ሲቲና በኖርዊች ሲቲ ቆይታ ያደረገ ሲሆን፥ የቶተንሃም ዋናውን ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ ታሪኮችን መፃፍ ችሏል።

ኬን በፕሪሚየር ሊጉ 213 ጎሎችን በማስቆጠር የምንጊዜም ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው፡፡

ጎሎችን ማስቆጠር የማይታክተውና በወጥነት አቋሙ ሳይዋዥቅ መጫወት የማይቸግረው ኬን በ31 ዓመቱ ትልቅ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ከባቫሪያኑ ጋር በማሳካት የዓመታት የዋንጫ ጥሙን ቆርጧል።

በስፖርት ቤተሰቡ ሁሌም ተናፋቂ የነበረው ሀሪ ኬን እና ዋንጫ መች ይታረቃሉ የሚለው ጉዳይ ዘንድሮ መልስ አግኝቷል።

ኬን እና ዋንጫም በአሊያንዝ አሬና ታርቀዋል።

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version