Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቀጣዩን ትውልድ የውሃ ዲፕሎማት፣ ተደራዳሪ እና ሳይንቲስት እንዲሆን ማሰልጠን ይገባል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀጣዩን ትውልድ የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማት፣ ተደራዳሪ እና ሳይንቲስት እንዲሆን ማሰልጠን እንደሚገባ የውሃና ኢኔርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገልጸዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የወሰን ተሻጋሪ የውሃ ትብብር ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርገው 12ኛው የውሃ እና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ በውይይት እና ግልጽነት ከጎረቤቶቻችን ጋር መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ቀጣዩን ትውልድ የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማት፣ ተደራዳሪ እና ሳይንቲስት እንዲሆን ማሰልጠን ይገባል ብለዋል።

ለትብብር ያለንን ቁርጠኝነት በማሳየት ዓለም አቀፍ ድጋፍን መሳብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ ቀጣይነት ያለው የውሃ ልማት ከዲፕሎማሲ ውጭ ሊሆን እንደማይችልና ዲፕሎማሲውም ያለመረጃ፣ እውቀት እና እምነት ውጤታማ እንደማይሆን አመላክተዋል።

ሀገራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ የወደፊት ሰላም፣ ትብብር እና የጋራ ልማትን ለመቅረጽ ራሳችንን ማትጋት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ የዘርፉ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ መሐንዲሶች፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

በመለሰ ታደለ

Exit mobile version