አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኅብረት ሥራ ማህበራት እና ዩኒየኖች አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኝ የሚያስችል ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጫልቱ ታምሩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ከወደብ ተጓጉዞ ወደ ሀገር የገባውን የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚው ለማድረስ የኅብረት ሥራ ማህበራት እና ዩኒየኖች የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ለ2017/18 ምርት ዘመን የሚውል 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እስካሁን መድረሱን ገልጸው፤ የኅብረት ሥራ ማህበራት እና ዩኒየኖች ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ጥናት ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር መከናወኑን አስታውሰው፤ በዚህም ከግብርና ኤክስቴንሽኖች፣ ከፀጥታ አካላትና ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት እና ዕቅድ በማውጣት የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ስርጭት እንዲቀላጠፍ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የኅብረት ስራ ማህበራት በማይደርሱባቸው አካባቢዎችም ግብርና ሚኒስቴር እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በዮናስ ጌትነት