Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሲዳማ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ ከ307 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 307 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

በክልሉ በአንድ ጀምበር ከ8 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ፍቅረየሱስ አሸናፊ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከተዘጋጁት 307 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞች መካከል 60 በመቶው ለምግብነት እና ለመኖነት እንዲሁም 40 በመቶው የደን ሽፋንን ከፍ ለማድረግ የሚውል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለችግኝ ተከላ የሚሆን 23 ሺህ 300 ሄክታር መሬት የቦታ ልየታ መደረጉን ገልጸው፥ የጉድጓድ ዝግጅት አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 70 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአጠቃላይ በክልሉ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፥ በዚህም የደን ሽፋንን 24 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

ክልሉ የበልግና የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ መሆኑን ያስረዱት ምክትል ሃላፊው፥ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቀደም ብሎ መጀመሩን ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በዚህ አመትም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version