አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል 142ኛ አባል ሀገር ሆና ተመዘገበች።
ከግንቦት 11ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሲሪላንካ ሲካሄድ የቆየው የዓለም አቀፉ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል 80ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቋል።
በጉባዔው ኢትዮጵያን በመወከል በመቻል ስፖርት ክለብ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሳቢ ሠይፉ ጌታሁን (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ተሳትፏል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል እንድትሆን የተለያዩ ምክንያታዊ ሃሳቦችን እንዳቀረቡ ተመላክቷል።
በዚህም የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በዓለም አቀፉ ወታደራዊ ስፖርት ካውንስል 142ኛ አባል ሆና መመዝገቧን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ሌተናል ኮሎኔል ውብሸት ቸኮል ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
ሠይፉ ጌታሁን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተልዕኮውን በሚገባ የሚፈጽምና የተሠማራባቸውን ግዳጆች በአሸናፊነት የሚያጠናቅቅ ነው።
ኢትዮጵያን በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በልበ ሙሉነት ከጥቃት እየተከላከለ ተከብራ እንድትኖር ያስቻለ የድል ሠራዊት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
መቻል ከክለብ አልፈው ሀገር ያስጠሩ እንደነ ባሻዬ ፈለቀ፣ ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ ሻምበል ማሞ ወልዴ፣ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርና ሌሎችንም ስመጥር ስፖርተኞችን ማፍራቱን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የስፖርት ካውንስሉ አባል ሀገር እንድትሆን በሃሳብ ለደገፉ ሃገራት፣ ለዓለም አቀፉ ወታደራዊ ስፖርት ም/ቤትና ለአፍሪካ ወታደራዊ ስፖርት ም/ቤት ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በአለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ አፈፃፀም የረጅም ዓመታት ታሪክ ያላት ተወዳጅ ጠንካራና በችግሮች የማይንበረከክ ሠራዊት መገንባት መቻሏ በጉባዔው ተገልጿል።
በመላኩ ገድፍ