አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 3 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ግጭት እንዳይከሰት ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ስራ በተግባር ላይ ማዋሉን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል÷ በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
አሰራሩ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥና ለፈጣን ምላሽ አሰጣጥ የሚያስችል ስርአት እንደሆነ ተናግረው÷ በሁሉም አካባቢዎች የሚታዩ የግጭት ምንጮች ላይ መረጃ በመሰብሰብ ቀድሞ ለማወቅና ለመተንተን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የኢንተርኔት ቴክኖሎጂው እስከሚስፋፋ የመረጃ መሰብሰብ ስራውን በሰዎች እንዲከናወን በማድረግ ግጭት ሳይፈጠሩ ቀድሞ የመከላከል ስራ መጀመሩንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ባለፈው አመት ግጭት በመፍጠር የተጠረጠሩ ግለሰቦች 87 በመቶ ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉንም ጠቁመው ÷ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በወንጀል የተጠረጠሩ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ጥረት እንደተጠናከረ ገልጸዋል።
ከዚያም ባለፈ በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ የአመለካከት፣ የብሄራዊ መግባባትና መሰል የሰላም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አንዳንድ የሰላም ግንባታ ስራዎች ውጤታቸው ቶሎ የሚታይ አለመሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ÷ ስራዎቹ በቀጣይ ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ጌቱ ተክለዮሃንስ በበኩላቸው÷ የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት በሙሉ አቅሙ የአገር ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ግዳጁን ለመወጣት የተለያዩ ግብዓቶች እየተሟሉለት እንደሆነ አመልክተዋል።
”ለረዥም ጊዜ ሲጓተቱ የነበሩ ስራዎች በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ነው” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ÷በተለይ ሰላም ከማስከበር አኳያ የተለያዩ አደረጃጀቶችን የመፍጠር ስራው እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከህዝብ ጋር በቅርበት በመስራት የተጀመረው የሰላም ማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

