Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቡና ጥራትን የማሻሻል ሥራ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ጥራትን ለማሻሻል ክልሎችን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የቡና ጥራትን ለማሻሻል ከተዋንያኑና ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ መሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታጋይ ኑሩ ተናግረዋል፡፡

የቡና አመራረት ፓኬጅ ተሻሽሎ ለሁሉም ተዋንያንና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ የ10 ዓመታት ስትራቴጂና ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

በጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ አዳዲስ ምርቶች በተሻለ ጥራት ወደ ገበያ መግባት ችለዋልም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የኮሜርሺያል ቡናዎች ድርሻ እየቀነሰ ስፔሻሊቲ ቡናዎችን በስፋት ወደ ገበያ በማቅረብ በተሻለ ዋጋ መሸጥ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አርሶ አደሩ፣ ላኪው እና ሀገር በይበልጥ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ከጥራት ጋር በተያያዘ 1 ሺህ 506 የታጠበ ቡና ማዘጋጃ እንዲሁም 1 ሺህ 10 ደረቅ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ለፋና ዲጂታል አስረድተዋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት፤ 208 ሺህ ቶን የታጠበ ቡና እና 325 ሺህ 500 ቶን ደረቅ ቡና ማዘጋጀት መቻሉን አንስተዋል፡፡

ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የቡና እደሳ ንቅናቄ በማድረግ፤ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደል፣ በአዲስ የመተካት እና ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሚመረተው ቡና አረቢካ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቡና ጣዕም እና ጥራት ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ ቡናን በጥላ ዛፍ መትከል (አግሮ ፎረስተሪ ሲስተም) በሥፋት እየተሠራበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version