አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመምህራን የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግስት በየደረጃው ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ መምህራን ጋር ባካሄዱት ውይይት መንግስት የትምህርት ዘርፉን የሚያጠናክሩ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም የተማሪዎች ምገባን ማስጀመር፣ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ማሳደግ፣ ለትምህርት ጥራት እንዲያግዙ የተለያዩ ግብዓቶችን ማቅረብ መንግስት የወሰዳቸው የማጠናከሪያ ርምጃዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የመምህራንን የመኖርያ ቤት ጥያቄ በሂደት ለመፍታት 350 ማህበራት ተደራጅተው ከ9 ሺህ የሚያልፉት ቁጠባ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከመምህራን የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግስት በየደረጃው ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በስራዎቻችን ሂደት የተመዘገቡ መልካም ነገሮችን በመነሳሻነት እየወሰድንና ክፍተቶችን እያረምን በመምጣችን ዛሬ በከተማችንና እንደ ሀገር የተመዘገቡ የልማት ስራዎች እውን ሆነዋል ብለዋል። ይህም የመጣው በዜጎች አጠቃላይ ጥረትና ርብርብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ በትምህርት ዘርፍ ላሳዩት ድጋፍም በአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማህበር እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በታምራት ደለሊ