አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸውን ሥፍራዎች ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት መምጣቱን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።
የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/11 አጫሽ ያልሆኑ ወገኖች ለትንባሆ ጭስ የነበራቸውን ተጋላጭነት መቀነስ ማስቻሉን የባለስልጣኑ የትምባሆ ቁጥጥር ዴስክ ኃላፊ ቶሎሳ ገመዳ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ትምባሆ ህዝብ በተሰበሰበበት ሥፍራ ያለክልከላ ይጨስ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ለመገደብ የወጣው አዋጅ አበረታች ውጤት ማምጣቱን ኃላፊው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ባልተፈቀዱ ሥፍራዎች ትምባሆ ማጨስ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተወገደ ጠቅሰው፤ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሆቴሎች፣ ድርጅቶችና የተለያዩ ተቋማት በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ኃላፊው ጠይቀዋል።
የአዋጁ አስፈፃሚ አካላት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ድርጊቱን በሚፈጽሙት ላይ አስተማሪ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በመሆኑም የችግሩ ባለድርሻ አካላት የሆኑት ተቋማት አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሰራተኞቻቸውንና ደንበኞቻቸውን ከሲጋራ ጭስ ተጋላጭነት መከላከል ተቀዳሚ ስራቸው ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ጠበቃ እና የህግ አማካሪዋ ህሊና ሽብሩ÷ በተከለከሉ ሥፍራዎች ትንባሆ ማጨስ በወንጀል ያስጠይቃል በማለት ገልጸዋል።
የትምባሆ ቁጥጥር ዋና አስፈፃሚዎች የሆኑ ተቋማት ደንቦችን በመተላለፍ ትንባሆ ሲያጨስ የተገኘን ግለሰብ በትምባሆ ቁጥጥር ሞዴል መመሪያ 771/2011 አማካኝነት በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በመሆኑም አስፈፃሚ አካላት ትምባሆ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት ግለሰቦች በዘፈቀደ ትንባሆ በሚያጨሱበት ጊዜ በአካባቢው ለሚገኙ ደንብ አስከባሪዎች ማሳወቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የትምባሆ ቁጥጥር አዋጁን ተግባራዊ በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም የህግ ባለሙያዋ መክረዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ