አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፡፡
በክልሉ ከጤና ባለሙያዎች ጋር “የጤና ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የማጠቃለያ ውይይት እየተካሄደ ነው።
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መንግስት በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን እና የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ለመፍታት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በዘርፉ እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ለሙያቸው የገቡትን ቃል በማክበር ሕዝባቸውን እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰው÷ ጥያቄያቸውን ጠልፈው የፖለቲካ መጠቀሚያ ለሚያደርጉ አካላት ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በፍሬው ዓለማየሁ