አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቢል ጌትስ የአፍሪካን ዘላቂ ድጋፍ እና ዓለም አቀፍ አጋርነት ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በህብረቱና በጌትስ ፋውንዴሽን ትብብር ዙሪያ ከቢል ጌትስ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የአፍሪካን ጤና ሥርዓትና የምግብ ዋስትና ማሳደግ እንዲሁም የሀገር ውስጥ የክትባትና የመድሃኒት ማምረቻዎችን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም መክረዋል፡፡
ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት፥ በተለይም የዓለም አቀፍ ድጋፎች መቋረጥና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ቃል የተገቡ ድጋፎች አለመፈጸማቸው ለአህጉሪቱ አሳሳቢ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ቢል ጌትስ በበኩላቸው የአፍሪካን ስጋት እንደሚጋሩ ገልጸው ፥ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ድጋፍና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች አስቸኳይ ዓለም አቀፋዊ ትብብር፣ ፍትሃዊ ንግድ፣ የእዳ እፎይታና አፍሪካ መር ፈጠራ አስፈላጊነት ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመላክታል፡፡