አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን አጠናቅቀው የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ወስደዋል አለ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ በክልሉ 767 ሺህ ዜጎችን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 192 ሺህ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ÷እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይም በክልሉ 129 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠናን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ፋይዳን ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቅርቡ ለዲጂታል መታወቂያ ግብዓት የሚሆኑ ቁሶች ለክልሉ ድጋፍ መደረጋቸውን ጠቁመው ÷ ይህም መታወቂያውን በሁሉም አከባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ የዲጂታል መታወቂያን ከባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ