አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ የአዋሽ ወንዝ መዳረሻ ላይ የሚገኘውን የአብዬ ሃይቅ የቱሪስት መዳረሻነት ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ መሐመድ አሊ ቢኢዶ ÷በ2017 በጀት ዓመት በአፋር ክልል ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በክልሉ የሚገኘውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በተለያዩ ዘዴዎች ለማስተዋወቅ በትብብር መሰራቱን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ በማልማት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በአዋሽ ወንዝ መዳረሻ ላይ የሚገኘውን የአብዬ ሃይቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም በአብዬ ሃይቅ የአስፋልት መንገድን ጨምሮ አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ መከናወኑን ነው ያብራሩት፡፡
የአብዬ ሃይቅ ከቱሪስት መስህብነት ባለፈ ለአሳ ምርት አገልግሎት እንዲውል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ÷ሃይቁን የማልማቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ