Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎች …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የወጪና ገቢ ምርቶችን ለመቆጣጠር በተለያዩ አካባቢዎች ካቋቋማቸው የፍተሻ ኬላዎች ውጭ ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎች መኖራቸው ተደጋግሞ ይነሳል።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት ከንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር በተወያዩበት ወቅት በዋናነት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የህገወጥ ኬላዎች ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡

ምርቶች ከወደብ ወደ መሃል ሀገር በሚጓጓዙበት ወቅት በግልጽ ከሚታወቁ የፍተሻ ኬላዎች ውጪ በህገወጥ መንገድ በተዘረጉ ኬላዎች ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እየተዳረግን ነው ብለዋል።

ከመንግስት ህጋዊ እውቅና ውጪ የፍተሻ ኬላዎች በመኖራቸው ምክንያት በወቅቱ ለገበያ መቅረብ የነበረባቸው ምርቶች እየዘገዩና አልፎም ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሆነም አንስተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ መንግስት ካቋቋማቸው የፍተሻ ኬላዎች ውጭ በየመንደሩ ገመድ እየዘረጉ የምርት አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡም በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ280 በላይ ህገወጥ ኬላዎች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎችን በመዘርጋት የንግድ ስርዓቱን የሚያውኩ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎችን ከመለየት ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፥ ክልሎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎችን ለማስወገድ እንዲቻል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በዋናነት ሰፊ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው፥ መሳሪያ እየታጠቁ ህገወጥ የፍተሻ ኬላዎችን በመዘርጋት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ማስቆም እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በህገወጥ የፍተሻ ኬላዎች እየተፈጸሙ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግስት ከሚወስዳቸው ርምጃዎች በተጨማሪ የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ መንገድን ብቻ በመከተል ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version