አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙኃን በአካባቢ ብክለት መከላከል ሀገራዊ ንቅናቄ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል አሉ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው።
ጽዱ ኢትዮጵያ በሚል መሪ ሐሳብ ለስድስት ወር የሚቆይ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በጽዱ ኢትዮጵያና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የመገናኛ ብዙኃን ሚና በሚል ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እንደገለጹት፥ መገናኛ ብዙኃን በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ዘመቻ ውስጥ በሐሳብ ቀረጻ የአንበሳውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
በንቅናቄው ውስጥ ያላቸውን ተደራሽነት በማሳደግና በጋራ ሐሳብና ዓላማ ማህበረሰቡን ያማከለና ያሳተፈ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
መገናኛ ብዙኃን መረጃ ከመስጠት ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ የባህል ለውጥ እስከሚመጣ ድረስ ልንተጋ ይገባል ብለዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፥ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል፡፡
መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ በፖሊሲና በተቋማት ያሳየውን ቁርጠኝነት ሚዲያዎች በሚሰሯቸው ስራዎች በኩል ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ሚዲያዎች በንቅናቄው ዘላቂ የሆነ ውጤት ለማምጣት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት