አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቅርሷንና ታሪኳን ለትውልድ ማስተላለፍ ያስቻለ ድንቅ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ገንብታለች አሉ የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርክ ሙሳር (ዶ/ር)፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረጉት ፕሬዚዳንቷ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ የድል መታሰቢያውን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ፤ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ በመዲናዋ የሚከናወኑ የኮንስትራክሽን ሥራዎች የሀገሪቷ ዕድገት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተለያዩ የትብብር መስኮች እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነው የዓድዋ ድል ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ እንደ ዓድዋ ያሉ የድል ታሪኮችን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ያከናወነችው ተግባር ይደነቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እያንዳንዱ ሀገር ቅርሱንና ታሪኩን መንከባከብ እንዳለበት በመጥቀስ፤ በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶቿን ለመመልከት ለሚመጡ ሁሉ ማሳየት የምትችልበት ድንቅ ሙዚየም እንዳላት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡