አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመልክዓ ምድር አመላካች ምርቶች ጥበቃ ሥርዓትን ለመተግበር በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን፡፡
የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤሊያስ መሃመድ እንዳሉት÷የመልክዓ ምድር አመላካችነት ማረጋገጫ ሥርዓት ለፍትሃዊ ንግድ ውድድር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ሥርዓቱ ጥራታቸው እና የገበያ ተፈላጊነታቸው ከሚመረቱበት አካባቢ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንደ አዕምሯዊ ንብረት ማስጠበቅ ያስችላል ብለዋል፡፡
በዚህም የምርቶችን እና አገልግሎቶችን የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንዲሁም የሸማቾችን ምርጫና ፍላጎት በማሟላት የተሳለጠ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠር ሚናው ጉልህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመገኛ ቦታቸው ተለይተው የሚታወቁ እንደ ቡና፣ ጤፍ፣ ቅቤ እና ሌሎች ተወዳጅ ምርቶች በመገኛ ቦታቸው መለያ ተሰጥቷቸው ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርቡ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
የመልክዓ ምድር አመላካችነት ማረጋገጫን መተግበር የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንደሚሳድግ አብራርተዋል፡፡
የማህበረሰቡን ዕውቀትና ባህልን ለመጪው ትውልድ ለማቆየትና ለማስጠበቅ ብሎም በንግድ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ ለመሆን ወሳኝ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የመልክዓ ምድር አመላካች ምርቶች ጥበቃ ሥርዓትን ለመተግበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ