Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክልሉ ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል።

የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ 34 ሺህ 254 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት 11 ወራት ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል።

የቡና ምርትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው÷ በዋናነትም የቡና ጥራት ማስጠበቅና ህገ ወጥነትን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በ11 ወራት ውስጥ ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በበጀት ዓመት ከታቀደው በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።

የቡና አምራቾች ካመረቱት ምርት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ መከናወኑንም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ ከደላላ ሰንሰለት ወጥቶ እራሱ በግብይት ማዕከላት ላይ መሸጥ እንዲችል ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ መሰራቱን የገለጹት አቶ አማኑኤል÷ ለዚህም በክልሉ የተዘጋጁ 543 የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላት መኖራቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ያቀፉ ዩኒዬኖች ቡናን ከማኅበራት ሰብስበው ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ከ850 በላይ ሁለትና ከዛ በላይ ሄክታር የቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ቀጥታ ወደውጭ ገበያ በመላክ እንዲሁም ከሌሎች የቡና ላኪ ነጋዴዎችና አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት ውጤታማነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version