አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የቱሪስት መስህቦችን፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ሰንዶ ለልጆች ማስተማር ይገባል አሉ።
በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ የተጻፉ ሁለት የሕፃናት መጻሕፍት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መጻሕፍቱ የቱሪዝም መስህቦችን፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን የሚዳስሱ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሀ፣ ሁ(ABC’s of Ethiopian Tourism) እና ABC Tuuriizimii oromiyaa በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ ናቸው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በመርሐ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ያላትን በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ይዘታቸውን ሰንዶ ለትውልድ በማስተላለፍ ልጆች ላይ መስራት ይገባል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት መጻሕፍት ልጆች የሀገራቸውን ታሪክና ባህል እንዲሁም የቱሪዝም ሀብቶች እንዲያውቁ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ መጻሕፍቱ የቱሪዝም ሀብቶችን ለትውልድ ማስተማር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም የቱሪዝም ሀብቶች ይዘታቸው ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መጻሕፍቱን ያዘጋጁት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ልጆች የሀገራቸውን የቱሪስት መስህቦች፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን ሊረዱት በሚችሉት ልክ የተዘጋጁ መጻሕፍት መሆናቸውን አመልክተዋል።