Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

315 የተሳካ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት 315 የተሳካ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ተሰጥቷል አለ።

በማህበረሰቡ ዘንድ እየዳበረ የመጣውን የደም እና የዐይን ብሌን ልገሳ ተግባርን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ሀገራዊ ንቅናቄ ”የህይወትና የብርሃን ስጦታ ያበርክቱ ደም ይለግሱ የዐይን ብሌን ይለግሱ” በሚል መሪ ሀሳብ በነገው ዕለት ይካሄዳል።

የአገልገሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ እንደገለጹት፤ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለያየ መልኩ ይሰጥ የነበረውን የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ወጥነት ባለው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ሥር እንዲሰጥ መደረጉን አስታውሰዋል።

ይህም የህክምና አገልግሎቱ ፍትሃዊና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ዓይነተኛ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት 315 የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ተሰጥቷል ብለዋል።

522 ሰዎች ደግሞ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ህክምናው በስፋት እየተሰጠ የሚገኘው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሆን ህክምናውን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ለአብነትም በሀዋሳ፣ በጎንደር፣ በጅማ እና መቀሌ ሆስፒታሎች ላይ የዐይን ብሌን ቀዶ ህክምናው እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

የዐይን ብሌን የማንሳት ሥራ በሚኒሊክ ሆስፒታል ብቻ እየተሰራ በኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልገሎት በኩል ለህክምና ተቋማቱ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመው፤ የዐይን ብሌን የሚሰበስቡ ተቋማትን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ጅማ ከተማ ላይ የዐይን ባንክ ተቋምን የማቋቋም ሥራ የተከናወነ ይገኛል በማለት ገልጸው፤ በቀጣይ በጀት ዓመት ተጨማሪ የዐይን ባንክ እንደሚኖር ይጠበቃል ብለዋል።

Exit mobile version