Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን የስደተኞች አካታች ፖሊሲ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ሊደግፉት ይገባል – ፊሊፖ ግራንዲ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት ነው ያሉትን የኢትዮጵያን አካታች የስደተኞች ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ሊደግፉት ይገባል አሉ።

ኢትዮጵያ እያሳየች ላለችው የስደተኞች አያያዝ አድናቆታቸውን የቸሩት ኮሚሽነሩ፥ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች በገንዘብ፣ በቴክኒክ እና በሌሎች አማራጮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻዎች በተገኙበት ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የስደተኞች ማካተት ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በመድረኩ ላይ፤ የተቋማቸው ቁልፍ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ስምምነት ጋር የተጣጣመ ዘላቂ፣ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎችን እየተገበረች እንደሆነ አንስተው፤ በህጋዊ ሰነዶች፣ በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እና በትምህርት፣ በጤና እና በገንዘብ አገልግሎቶች ስደተኞችን ተጠቃሚ በማድረጓ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረው ከተረጅነት በመላቀቅ በምግብ ራስን የመቻልና ፈተናዎችን የሚቋቋም ስርዓተ ምግብ እውን የማድረግን ጉዞ አድንቀው፥ ሀገራት ተሞክሮውን ሊወስዱት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በስደተኞች ዙሪያ እየተተገበረ ያለው የ”ማካተት” ሞዴል ተጨባጭ ውጤት በማምጣቱ ወደ ሌሎች ሀገራት መስፋት አለበት ብለዋል።

ከለጋሽ አካላት የሚገኘው የሠብአዊ እርዳታ መቀነስ በስደተኞችና በተቀባይ ማህበረሰብ ላይ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ጫናዎችም ጠቅሰው፤ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች የኢትዮጵያን ፈር ቀዳጅ የስደተኞች አካታችነት ተግባራትን እንዲደግፉ ጠይቀው፤ ኢትዮጵያ የድርሻዋን እየተወጣች ነው፤ ባለድርሻ አካላት ደግሞ ድርሻቸውን ይወጡ ብለዋል።

በመሳፍንት ብርሌ

Exit mobile version