Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን እንድታጠናክር በር ከፍቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን እንድታጠናክር በር ከፍቷል አለ።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳ ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ ብልጽግና ምልክት እንድትሆን ማስቻል ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ስኬት ከግምት አስገብቶ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ያማከለ እና የወደፊት መድረሻ ላይ ትኩረት ያደረገ ማሻሻያ መሆኑ ይታወቃል።

የገንዘብ ሚኒስትር አማካሪ ፍሬህይወት አንዳሞ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ማሻሻያው የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና በአይሲቲ ዘርፎች ላይ እየሰራ ይገኛል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል ወሳኝ ሚና መጫወቱን ገልጸው፤ ከዚህ ባለፈ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን እንድታጠናክር በር ከፍቷል ብለዋል፡፡

ማሻሻያው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ፀጋዎች በመለየት ለውጭ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ሀገራት በዓለም መድረክ ላይ ተደማጭነት እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበር የዘርፉ ተመራማሪ አቡሌ መሀሪ (ዶ/ር) ናቸው።

በኢኮኖሚ ራሱን የቻለ ሀገር ከተረጂነት ከመላቀቅ በላይ ጥቅሙን ማስጠበቅ እና ተደማጭነቱን ማስፋት ይችላል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማለት በኢኮኖሚ ራስን መቻል ብቻ አይደለም ያሉት ተመራማሪው÷ ሀገራት በዓለም የንግድ መስተጋብር ውስጥ በመሳተፍ ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገራት የገበያ መዳረሻቸውን በማስፋት ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉበት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version