አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2017 በጀት ዓመት ቀሪ ገቢን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ለመሰብሰብ ባለድርሻ አካላት በመናበብና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
በመዲናዋ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ ላይ ያተኮረ ግምገማ መካሄዱን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የ90 ቀናት የትኩረት አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን፥ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ዝርዝር የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ገቢን የመሰብሰብና ለልማት የማዋል ብቃት እየዳበረ መምጣቱ በመዲናዋ እየተመዘገቡ ላሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ዋነኛው መሰረት መሆኑ በግምገማው መድረክ ላይ ተነስቷል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት፥ የ2017 በጀት ዓመት ቀሪ ገቢን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ አጠናቅቆ መሰብሰብ ለቀጣዩ በጀት ዓመት መሰረት መሆኑን አንስተው÷ ይህንን ለማሳካት ባለድርሻ አካላት ተናብበንና ተቀናጅተን በጋራ መስራት ይገባናል ብለዋል።
እንዲሁም ለ2018 በጀት ዓመት አመቺ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋት፣ ግብር ከፋዩን ማበረታታት እና ሰራተኛውን ማትጋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በኃይለማሪያም ተገኝ