አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት እየተካሄደ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ሞዴል የገጠር መንደሮቹ ቀላል ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ እንዲሁም አርሶ አደሩ ጤናማ እና ክብር ያለውን ህይወት እንዲኖር እንደሚያስችሉ መግለፃቸው ይታወቃል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ አራት ዞኖች በሚገኙ አራት ወረዳዎች የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳላቸው ጠቁመው÷ ይህም ዘላቂ ልማትና የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።
በአራት መንደሮች የተጀመሩ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ለሌሎች አካባቢዎች ሞዴል በሚሆኑበት መንገድ በሁለት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በፍጥነት እና በጥራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው የገጠሩ አካባቢ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አስታውሰው፤ የኮሪደር ልማቱ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን እንደሚፈጥር እና የአርሶ አደሩን ህይወት እንደሚቀይር ተናግረዋል።
የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ከተማ የሚሄደውን አርሶ አደር በሚኖርበት ተረጋግቶ እሴት ጭመራ ላይ እየሰራ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
የገጠር ኮሪደር አጠቃላይ የኅብረተሰብ ሽግግርን የሚያመጣ እና መሰረተ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮችን ያቀፈ እንደሆነ ገልጸዋል።
ልማቱን የአካባቢው ኅብረተሰብ በባለቤትነት እያገዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ኡስማን÷ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የመንግስት መዋቅር በተቀናጀ መንገድ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ማስጀመራቸው በአመራሩ እና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠሩ ሁሉም አካላት ገንዘብ እና ጉልበትን ጨምሮ የተለያየ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!