አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩክሬናዊው የቼልሲ ክንፍ ተጫዋች ሚካዬሎ ሙድሪክ ያልተፈቀደ አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀም በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ክስ ቀርቦበታል፡፡
የ24 ዓመቱ ተጫዋች ከአበረታች ንጥረ ነገር ጋር ተያይዞ ካሳለፍነው ታሕሳስ ወር ጀምሮ ከእግር ኳስ ውድድሮች መታገዱ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይም ሙድሪክ ያልተፈቀደ አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀም ከእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ክስ እንደቀረበበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተጫዋቹ አበረታች ንጥረ ነገሩን ሆን ብሎ መጠቀሙ ከተረጋገጠ እስከ አራት ዓመት የሚደርስ የእግር ኳስ እገዳ ሊጣልበት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
ሙድሪክ በፈረንጆቹ 2023 ነበር ከሻክታር ዶኔስክ ቼልሲን በ89 ሚሊየን ፓውንድ የተቀላቀለው፡፡