Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የክለቦች ዓለም ዋንጫ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ወደ 32 ከፍ በማድረግ ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት የተጀመረው የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡

በስምንቱ ምድቦች በተደረጉ 16 ጨዋታዎች በድምሩ 44 ግቦች ሲቆጠሩ፥ 6ቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል፡፡ በእነዚህ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች 5 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡

ሻቢ አሎንሶ የሪያል ማድሪድ የአሰልጣኝነት ስራቸውን ከሳዑዲ ፕሮ ሊጉ አል ሂላል ጋር አቻ በመለያየት ጀምረዋል፡፡ 1 ለ 1 አቻ በተጠናቀቀው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጎንዛሎ ጋርሲያ ለሪያል ማድሪድ እንዲሁም ሩበን ኔቬሽ ለአል ሂላል ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡

በዚህ የዝውውር መስኮት ከሊቨርፑል ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ለሎስ ብላንኮዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል፡፡ በዚሁ ምድብ የኦስትሪያው አርቢ ሳልዝበርግ የሜክሲኮውን ፓቹካ 2 ለ 1 በማሸነፍ ምድቡን እየመራ ይገኛል፡፡

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም በዝውውሩ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቼስተር ሲቲ በምድብ 7 ከሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር ተገናኝቶ ፎደንና ዶኩ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2 ለ 0 በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምሯል፡፡

በዚሁ ምድብ ዩቬንቱስ የዩናይትድ አረብ ኢምሬትሱን አል ዐይን 3 ለ 0 በማሸነፍ ከሲቲ በግብ ክፍያ በልጦ ምድቡን መምራት ጀምሯል፡፡

ቼልሲ በተመሳሳይ ፔድሮ ኔቶ እና ኢንዞ ፈርናንዴዝ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሎስ አንጀለስ ኤፍሲን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ከሳምንታት በፊት ኢንተር ሚላንን በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካው ፒኤስጂ በክለቦች ዓለም ዋንጫ መድረክ የሊውስ ኤንሪኬው ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ 0 በመርታት አጀማመሩን አሳምሯል፡፡

ባየርን ሙኒክ በውድድሩ የኦሺኒያ አህጉርን በብቸኝነት የወከለውን የኒውዚላንዱ ኦክላንድ ሲቲ 10 ለ 0 የረመረመበት ጨዋታ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት መርሐ ግብር ሆኗል፡፡ በውድድሩ ከባቫሪያኑ ጋር የመጨረሻ ቆይታውን እያደረገ የሚገኘው ቶማስ ሙለር በክለቡ ቆይታው 250ኛውን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ሊዮኔል ሜሲን የያዘው ኢንተር ማያሚ ከአፍሪካ አህጉር ተወካዩ የግብጹ አል አህሊ ጋር ያደረጉትን የመክፈቻ ጨዋታ ጨምሮ ፍሉሚነንስ ከቦርሺያ ዶርትመንድ፣ ፓልሜራስ ከፖርቶ ያለግብ አቻ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

ሌሎች አፍሪካን የወከሉት ኢስፔራንስ ዴ ቱኒዝ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ በተመሳሳይ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል።

የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለው ብቸኛ የአፍሪካ ተወካይ ሆኗል፡፡

በተመልካቾች እጦት የደበዘዘ ነው በሚል እየተተቸ የሚገኘው ውድድሩ ዛሬም ሲቀጥል የምድብ 2ኛ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይጀምራሉ፡፡ በምድብ 1 ፓልሜራስ ከአል አህሊ ምሽት 1 ሰዓት እንዲሁም ኢንተር ማያሚ ከፖርቶ ምሽት 4፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

በምድብ 2 ደግሞ ሌሊት 7 ሰዓት አትሌቲኮ ማድሪድ ከሲያትል ሳውንደርስ እንዲሁም ሌሊት 10፡00 ፒኤስጂ ከብራዚሉ ቦታፎጎ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version