Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ሚናዋን እየተወጣች ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤ ምሲ) የአፍሪካ አህጉር ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ለማሳካት ኢትዮጵያ ድርሻዋን እየተወጣች ነው አሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የአውሮፓ ህብረት ‘ኢኮትሬድ’ የተሰኘ ፕሮጀክትን በኢትዮጵያ ባስጀመረበት ወቅት ነው።

የአራት ዓመት ቆይታና የስድስት ሚሊየን ዩሮ ፈንድ ያለው ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያግዛል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳመላከቱት÷ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ መርህ በመተግበር ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።

የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ጥምረት እውን እንዲሆን ብሔራዊ የትግበራ ኮሚቴ በማቋቋም እየሰራች መሆኑን ገልጸው÷ የአውሮፓ ህብረት ይፋ ያደረገው ‘ኢኮ ትሬድ’ ፕሮጀክትም ሂደቱን ያግዛል ብለዋል።

ህብረቱን ጨምሮ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ሚና የነበራቸው አካላት በኢትዮጵያ አቅም ላይ ላሳዩት መተማመን ምስጋና አቅርበው፤ ለውጤታማነቱ በትኩረት እንደሚሰራ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ኤሚስበርገር÷ የግሉን ዘርፍ አቅም ማጠናከር፣ የንግድ መርሁን ከአህጉራዊ ስምምነት ጋር ማያያዝ እንዲሁም ቀጣናዊ የንግድ ጥምረትን ማሳደግ ላይ ፕሮጀክቱ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።

በሚኪያስ ዓለሙ

Exit mobile version