Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢራን ግዙፍ የኒውክሌር ማዕከል ላይ በድጋሚ ጥቃት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን ግዙፍ የኒውክሌር ማዕከል የሆነው ፎርዶው በዛሬው ዕለት በድጋሚ ጥቃት እንደተፈጸመበት የአካባቢው ባለስልጣናት ተናገሩ፡፡

አሜሪካ በትናንትናው ዕለት ፎርዶውን ጨምሮ ናታንዝ እና ኢስፋሃን በተሰኙ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተሳካ የቦምብ ጥቃት መፈጸሟን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለት በድጋሚ በግዙፉ ፎርዶው የኒውክሌር ማዕከል ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ኮም በተሰኘው የኢራን ግዛት የሚገኘው የኒውክሌር ማዕከሉ ዛሬ አዲስ ጥቃት እንደተፈጸመበት የግዛቲቱ የአደጋ መከላከል ባለስልጣን ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ እና ያስተናገደውን ጉዳት በተመለከተ ቃል አቀባዩ ያሉት ነገር የለም፡፡

አሜሪካ ከፈጸመችው ጥቃት በኋላ ፎርዶው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ተናግረዋል፡፡

የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ለማወቅ እንዲቻልም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሜሪካ በሦስት የኢራን ኒውክሌር ማዕከላት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የቀጣናው ውጥረት ይበልጥ የተባባሰ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለትም ኢራን እና እስራኤል የአየር ጥቃት መፈጸማቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በዚህ መሰረትም የእስራኤል ጦር በተለይም በቴህራን የሚገኘውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ማዘዣ ማዕከል ኢላማ በማድረግ የሚፈጽመው የአየር ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ኢራን በዛሬው ዕለት በደቡባዊ እስራኤል ከፍተኛ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ነው የተገለጸው፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version