አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዘሃን የሚሰራጩ መረጃዎች ተገቢነት የላቸውም አለ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያቀረበው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ ቤት መቅረቡ እና ምክር ቤቱ ለሰው ሃይል፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል።
ረቂቅ አዋጁ በውጭ ሀገራት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንን መብት፣ ደህንነት እና ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሕጋዊ የሥራ ስምሪቱን ለማበረታታትና የዜጎችን መብት ደህንነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ሀገር ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪቱን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
የረቂቅ አዋጁ ግብና ዓላማም የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ክብርና እና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገወጥነቶችን መግታት እና ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡፡
ደረጃ ያለው የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን÷ ኤጀንሲዎች በሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛት፣ ክህሎት፣ የሙያ ዘርፍ፣ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተያያዥ መስፈርቶችን ታሳቢ በማድረግ ደረጃ የሚሰጥ ነው።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኤጀንሲዎች በባንክ ዝግ አካውንት እንዲያስቀምጡ የሚገደዱት ዝቅተኛ ገንዝብ ከ100 ሺህ ወደ 50 ሺህ ዶላር ዝቅ እንዲል አድርጓል።
እንዲሁም ጥብቅ የፋይናንስ ቁጥጥሮች ኤጀንሲዎች ለዋስትና የሚያስይዙት ገንዘብ በካሽ በባንክ እንዲቀመጥ የሚያስገድድ ሲሆን÷ ይህ ገንዘብ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የሚውል እንደሆነ እና ኤጀንሲዎች ለላኳቸው ዜጎች ተገቢውን ሃላፊነት እንዲወስዱ የሚያደርግ ነው።
ረቂቅ አዋጁ በዘርፉ የሚደረገው የሥራ ስምሪት፣ የስልጠና ምደባ፣ የብቃት ምዘናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ግልጽና ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ የአሰራር ሥርዓት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በአጠቃላይ በዜጎች መብት፣ ክብርና ደህንነት ላይ በመደራደር ሃብት ያጋብስ የነበረውን ሃይል የሚገታ ብቻ ሳሆን በየደረጃው የዜጎችን እና የሀገርን ጥቅም ሲጎዱ የነበሩ ሕገወጥ የጥቅም ማጋበሻ ሰንሰለቶችን በመበጣጠስ ሕጋዊ አሰራርን የሚያሰፍን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ በተለያዩ የመገናኛ ብዘሃን አውታሮች የተሰራጩ መረጃዎች ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል፡፡