አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በልዩ ልዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያለውን ከፍተኛ ብቃትና መልካም አፈጻጸም አድንቋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በተባበሩት መንግስታት የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ማርሴል አክፖቮ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ማርሴል አክፖቮ በዚህ ወቅት÷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በልዩ ልዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያለው ከፍተኛ ብቃትና መልካም አፈጻጸም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን ለማዘመን እያከናወነችው ያለው ሥራ ለሌሎች ሀገራት አርአያ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡
ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
የተባበሩት መንግስታት በዘርፉ በሚከናወኑ ሌሎች ተግባራት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እያከናወነ የሚገኘው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በአቅም ግንባታና ስልጠና ዘርፎች በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በመላኩ ገድፍ