አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል አሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ።
የምስራቅ አፍሪካ የውሃ እና መሠረተ ልማት ጉባኤ እንዲሁም የቢግ-5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ዐውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች ፊት እየቀደመ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ዘርፎችን እያስተሳሰረና እንዲነቃቁ እያደረገ ነው ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ግዙፍ ካፒታል የሚንቀሳቀስበት፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚያሳትፍና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ዘርፉ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የባቡር መሰረተ ልማት፣ የገበታ ለትውልድና ገበታ ለሀገር እንዲሁም ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከዚህ በላይ እንዲያድግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅርበትና በቅንጅት እንዲሰሩ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
በመሳፍንት ብርሌ