Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢራን አየር ክልሏን በከፊል ክፍት አደረገች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ከእስራኤል ጋር የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ የአየር ክልሏን በከፊል ክፍት አድርጋለች፡፡

እስራኤልና ኢራን ባለፉት 12 ቀናት ባካሄዱት ጦርነት ኢራን የአየር ክልሏን ሙሉ በሙሉ መዝጋቷ ይታወሳል፡፡

ጦርነቱ በአሜሪካ አሸማጋይነት በተኩስ አቁም ስምምነት የተቋጬ ሲሆን÷ ስምምነቱን ተከትሎ ቀደም ሲል እስራኤል የጦርነት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጇን በማንሳት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሳለች።

ኢራንም በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት የአየር ክልሏን በከፊል ክፍት ማድረጓ ተስምቷል፡፡

የኢራን መንገዶች እና ከተማ ልማት ሚኒስትር ቃል አቀባይ መጂድ አክቫን÷ በኢራን ምስራቃዊ ክፍል የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲደረጉ ተፈቅዷል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቴህራን መህራባድ እና ሆሚኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረጉ በረራዎች ላይ የተደረገው ክልከላ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት በሚኖረው አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት ኢራን የአየር ክልሏን ሙሉ በሙሉ ክፍት ልታደርግ ትችላለች ማለቷን ቲ አር ቲ ወርልድ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version