Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመታር የፀሀይ ኃይል ማመንጫ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል በኑዌር ዞን ዋንቶዋ ወረዳ በ96 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የመታር የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ የፀሀይ ኃይል ማመንጫው 250 ኪሎ ዋት ኃይል በማንጨት ከ2 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለገጠሩ ማህብረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የተገነባ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም ነዋሪዎች፣ ማህበራዊ ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛሉ ብለዋል።

በገጠር ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለማስፋት በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ 240 ሺህ ዜጎችንና ተቋማትን በፀሀይ ኃይል አማካኝነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጋትልዋክ ሪዮን በበኩላቸው፤ የተመረቀው ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ላልነበራት መታር ከተማ ማኅበረሰብ ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኤሌክትሪክ ኃይል ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ኃይል እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር፥ የፀሀይ ኃይል ማመንጫው በአፍሪካ ልማት ባንክና በፌዴራል መንግስት ድጋፍ ተደርጎ መገንባቱን ገልጸው፥ የአካባቢው ማህበረሰብ ለፕሮጀክቱ ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በኤፍሬም ምትኩ

Exit mobile version