Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን ማጠናከር ችላለች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንጎላ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን የሚያጠናክር ውጤታማ ተሳትፎ አድርጋለች አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

በሚኒስቴሩ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘርይሁን አበበ እንዳሉት ÷ ጉባዔው ኢትዮጵያ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጋር የተሰናሰለውን የቢዝነስ ዲፕሎማሲዋን ያጠናከረችበት ነው።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከአንጎላው ፕሬዚዳንትና ከወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጆ ሌሬንሶ እና ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎስና የአፍሪካ ኮርፖሬት ካውንስል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሎሪ ሊዘር ጋር መምከራቸውን ጠቅሰዋል።

ከዋናው ጉባዔ ጎን ለጎን በነበሩ የተለያዩ መድረኮች ፕሬዚዳንት ታዬን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በኩል ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም ማንጸባረቅ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በተለይ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳየችባቸው፣ የዘርፉን የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስተዋወቀችበት፣ የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ትስስር ምን መምሰል እንዳለበት እይታዋን ያካፈለችባቸው መድረኮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የጀመረቻቸውን ሰፋፊ ጥረቶች ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።

ሥምምነቱ ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል የያዘ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም ኢትዮጵያ የቱሪዝም መሰረተ ልማት በማስፋፋትና መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት ምቹ ለማድረግ የያዘችውን ውጥን እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በተጓዳኝም በጉባዔው የተለያዩ የግንኙነት መረቦች መዘርጋታቸውን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት፡፡

የኢትዮጵያ ልዑክ በዚህ ጉባዔ ላይ መሳተፉ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዲፕሎማሲ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ መጠቆማቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።

ጉባዔው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጥረቶች ለማጠናከር ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ÷ በዋናነት ለኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ በማፈላለግ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል በማስፋትና፣ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን በማፈላለግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version