አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የክረምት መርሐ ግብር 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኝ እየተተከለ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በቢሮው የቡናና ሻይ ዳይሬክተር ታከለ ሃይለማርያም ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በዘንድሮው የክረምት መርሐ ግብር 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
እቅዱን በስኬት ለማከናወንም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር መሬት በቡና መሸፈኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ÷ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታሩ ምርት በመስጠት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ቀደም ሲል በቡና ምርት ከሚታወቁት አካባቢዎች በተጨማሪ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖችም በቡና ምርት መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለቡና ምርት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት አቶ ታከለ÷ ቡናን በክላስተር ከማልማት ባለፈ ያረጁ የቡና ችግኞችን በአዲስ የመተካት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ቡናን በብዛት እና በጥራት በማምረት እሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡
በአቤል ንዋይ