አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ከ7 ሺህ 200 በላይ የግብርና ባለሙያዎች በቀበሌ ተሰማርተው ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ ነው አለ።
በክልሉ “የበለፀገ ቤተሰብ ለማየት እተጋለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ በግብርና ሴክተር እና በግብርና ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎች ዙሪያ ለባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በመድረኩ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር÷ ባለፉት የለውጥ አመታት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና ለማሸጋገር በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ልማት ባለሙያዎችን ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ በክልሉ ከ7 ሺህ 200 በላይ የግብርና ባለሙያዎች ተሰማርተው ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ እየሰጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ባለሙያዎቹ በሌማት ትሩፋት እና በሌሎች አዳዲስ ኢኒሼቲቮች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት፡፡
በተጨማሪም ባለሙያዎች በግብርናው ዘርፍ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት እንዲሁም አዳዲስ የግብርና ምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡
የድህነታችን ምክንያት ፀጋችንን በማወቅ ያለማልማት ነው ያሉት አቶ ኡስማን÷ እንደ ሀገር የተጀመረውን የግብርና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመቅደስ አስፋው