አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የ90 ቀን ልዩ የንቅናቄ አጀንዳ አካል የሆነው የፅዱ ኢትዮጵያ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ “ፅዱ፣ ውብ እና ደህንነቷ የተጠበቀች አዲስ አበባ” በሚል መሪ ሀሳብ በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የሁሉም ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከብክለት የጸዳ አካባቢያዊ ሥርዓተ ምህዳር እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ ንቅናቄው መዲናዋን ፅዱና ከብክለት የፀዳች በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
ንቅናቄው ህዝቡ በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ዕድል መፍጠሩን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአካባቢ ጥበቃና በብክለት ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በንቅናቄው እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በንቅናቄው የአፈር፣ የውሀ፣ የፕላስቲክ፣ የአካባቢ ብክለትን ለማስቀረት የጽዳት ዘመቻ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች ተግባራት ይከናወናሉ።