አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሻሻለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ ተከናውኗል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማንሰራራት የሚያሳልጥ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን ከዚህ ቀደም ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 22 በመቶ ማደጉን አንስተው፤ ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጨባጭ ውጤትን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከማዘጋጀት እስከ መንከባከብ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በአዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከወንዝ ዳር ልማት ጋር በማስተሳሰር እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በተለይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጎ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
በከተማ ደረጃ በነገው ዕለት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን እንደሚያስጀምር ገልጸው፤ ነዋሪዎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።