አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ከሊዮኔል ሜሲው ኢንተር ማያሚ የሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይጠበቃል፡፡
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ የሶስትዮሽ ዋንጫ አሸናፊው ፒኤስጂ ምድቡን በ6 ነጥብ የበላይ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን በውድድሩ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ኢንተር ማያሚ በበኩሉ በምድብ አንድ በፓልሜራስ በግብ ክፍያ ተበልጦ በ5 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጥሎ ማለፉን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
በፓሪሱ ክለብ የሁለት አመት ቆይታ የነበረው አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ከቀድሞ ክለቡ ጋር ጥሩ ትዝታ የለውም፡፡
ምንም እንኳን ማያሚ ፒኤስጂን ጥሎ ወደ ሩብ ፍጻሜው የማለፍ ቅድመ ግምት ባያገኝም፥ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ሜሲ ከቀድሞ ክለቡ ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ከወዲሁ ትኩረት ስቧል፡፡
በሌላ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት የብራዚሉ ፍላሚንጎ ከባየርን ሙኒክ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ትናንት ምሽት በተደረጉ የክለቦች አለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ቼልሲ የፖርቹጋሉን ቤኔፊካ በጭማሪ ደቂቃ 4 ለ 1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡
እንዲሁም ሁለቱን የብራዚል ክለቦች ባገናኘው ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፓልሜራስ ቦታፎጎን በማሸነፍ 8ቱን የተቀላቀለ ሲሆን በሩብ ፍጻሜው ከቼልሲ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
በአቤል ንዋይ