አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት እና በእርጅና ምክንያት በፈረሰዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ህንጻ ምትክ አዲስ ሁለገብ ህንፃ ገንብቶ አስረክቧል።
ሁለገብ ህንፃዉ በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት በመባል በሚታወቀዉ የቤተክርስቲያኗ ይዞታ ላይ የተገነባ ነዉ።
በከተማ አስተዳደሩ በጀት ደረጃዉን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ በዛሬዉ ዕለት የተመረቀዉ ህንፃ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
በርክክብና በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ ህንፃ የመተማመንና የመተባበር ውጤት ነው ብለዋል።
የቀድሞዉ ህንፃ ረጅም ጊዜ ያገለገለ በመሆኑ እርጅና ተጭኖት ነበር በማለት አስታውሰው፤ ህንፃዉ ያለበት አካባቢ ታሪካዊ በመሆኑና አሁን ካለው የአካባቢዉ ገፅታ ጋር የሚመጣጠን ዘመናዊ ህንፃ እንዲሆን ታስቦ ተገንብቷል ነው ያሉት።
የተሰራዉን ሥራ በማድነቅ ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና ያቀረቡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ወደፊት ለሀገርም ለቤተክርስቲያን የተሻለና ያማረ ሥራ እንዲሰራ እንመኛለን ብለዋል ።
ቤተክርስቲያኗ ለከተማዉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእዉቅና የምስክር ወረቀት አበረከተዋል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ