አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መሠረተ ልማትን ለማጠናከር የሚውል የ400 ሺህ ዶላር ድጋፍ አፅድቋል፡፡
ድጋፉ በአፍሪካ ልማት ባንክ በሚተዳደረው ካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ በኩል ከተለያዩ ለጋሽ አካላት የተገኘ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከፍተኛ አማካሪ አቶ አሰፋ ሱሞሮ ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ ድጋፉ ለህዝቡ እና ለካፒታል ገበያ ተዋናዮች መረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር ይውላል፡፡
ይህም የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለህዝቡ፣ ለባለሀብቶች እና ለሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች መረጃ ተደራሽ እንዲያደርጉ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ድጋፉ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች የሚሰጠውን ግብይት በተመለከተ ግልፅ እና ታማኝነት ያለው መረጃዎችን ተደራሽ ለማደረግ እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም ድጋፉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን የምርት ልውውጥ ለማጠናከር፣ የምርት አቅርቦቶችን ለማብዛት እና የአክሲዮን ገብያ ሽያጭን ለማሳደግ ይውላል ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በፈረንጆቹ 2019 በአፍሪካ ልማት ባንክ ስር የተቋቋመው የካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የካፒታል ገበያ ተቋማት ሲደግፍ የቆየ ሲሆን፤ እስካሁን ለ16 የአፍሪካ ሀገራት የ6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የባንኩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ