Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ 562 ነዳጅ ማደያዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በመሰማራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ችግር በፈጠሩ 562 የነዳጅ ማደያዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃ ተወስዷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች፣ የነዳጅ አጓጓዦች እና ኩባንያዎች ጋር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በሕገወጥ መንገድ ሰው ሰራሸ የነዳጅ እጥረት በመፍጠር ችግር እየፈጠሩ ባሉ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባው ነዳጅ ለዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና ለኢኮኖሚ ወሳኝ የመሆኑን ያህል ያለአግባብ ለመክበር በነዳጅ ላይ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ ባደረገው ክትትል በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ተሰማርተው ባገኛቸው 562 ነዳጅ ማደያዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመዋል።

ከ222 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ጠቅሰው÷ 54 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው መጠየቃቸውንና በሕገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መወረሱን አንስተዋል።

በቀጣይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የነዳጅ ስርጭት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚተገበር ገልጸው፥ ሕግን አክብረው በመስራት የሀገር ባለውለታ የሆኑ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።

በዚህም በሀገሪቱ ነዳጅ እያቀረቡ ባሉት 60 የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ÷ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የጋራ ስራዎች ይተገበራሉ ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው÷ በመዲናዋ የነዳጅ አቅርቦት ላይ በየቀኑ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአግባቡ ሕዝቡን በማያገለግሉ አካላት እና ግብይቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማይፈጽሙት ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version