አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ1 ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የድጋፍ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገትን ለማገዝ እንደሚውል ተመላክቷል፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማሪያም ሳሊም ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ መጠቀሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ በሚተገብረው መርሐ ግብር ማዕቀፍ መሰረት ስምምነቱ በድጋፍ እና በተራዘመ ብድር አማካኝነት የቀረበ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት፣ የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ ዘላቂ የማህበራዊ አገልግሎትን ለማረጋገጥና ሌሎች የሪፎርሙን ቁልፍ ተግባራትን ለመደገፍ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡