አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በሲዳማ ቡና፣ መቻል እና ሀዋሳ ከተማ ክለቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ሶስቱ ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች ክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያን በመተላለፍ እግድ ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል ቢያንስ አንዱን አሰልፈው ስለማጫወታቸው ጨዋታውን ከመሩት ዳኞች በቀረበው ሪፖርት ተረጋግጦ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ኮሚቴው ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት ክለቦቹ ተጫዋቾቹን በመጠቀም ያደረጓቸውን ጨዋታዎችን በፎርፌ እንዲሸነፉ በዚህም ለተጋጣሚዎቹ በሙሉ 3 ነጥብና 3 ንጹህ ግቦች እንዲሁም ለሶስቱ ክለቦች ደግሞ በእያንዳንዱ ጨዋታ 0 ነጥብ እና 3 የግብ እዳ እንዲመዘገብ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወስኗል።
በተሰጡት የፎርፌ ውሳኔዎች መሰረት የ2017 የፕሪሚየር ሊግ ደረጃና ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃ መስተካከሉንም ነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ ውድድር አመራርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ያስታወቀው፡፡