Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ።

የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የግብር ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብር በሙሉ አቅም መሰብሰብ አለበት።

ለዚህም በግብር አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በመፍታት የክልሉን ገቢ ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም ህገ-ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን በመከላከል፣ ሌብነትንና ያለ ደረሰኝ በሚገበያዩ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ በዘርፉ ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ግብር ከፋዩ በአግባቡ ግብር በመክፈል ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ3 ቢሊየን 104 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት አመት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ በታማኝነትና በወቅቱ ግብር ለከፈሉ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷል።

በተስፋዬ ኃይሉ

Exit mobile version