Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከድህነት ለመውጣት ትልቅ መሰረት ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ምርታማነትን በማሳደግ ከድህነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መሰረት ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፡፡

በአማራ ክልል”በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ አቦላ ተፋሰስ ላይ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ አቶ አረጋ ከበደ÷ አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በማስተካከል፣ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ ምርታማነትን በማሳደግ የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ እና ከድህነት ለመውጣት ትልቅ መሰረት ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ ልማት ሥራውን ውጤታማነት ለማስቀጠል በቋሚነት ህብረተሰቡን በሙሉ አቅም ማሳተፍ እንዲሁም የተቋማትን ቅንጅታዊ አሠራር ማስፋት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

እስካሁን 1 ነጥብ 55 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቅሰው÷205 ሺህ ሄክታር መሬት የተከላ ቦታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ለደን፣ ለፍራፍሬ፣ ለመኖና ለአፈር ለምነት ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ይተከላሉ ነው ያሉት።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ ላለፉት ሰባት ዓመታት በተሰራው ሥራ የማይቀለበስ የአረንጓዴ ልማት ላይ መድረስ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሠራርን በማሳደግና የተተከሉ ችግኞችን በቋሚነት በመንከባከብ ሁለንተናዊ ለውጡን ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።

በደሳለኝ ቢራራ

Exit mobile version